Header image  

Ethiopian Music Legend

1940-2009

 
 
 

Tilahun Gesesse's Links

ኩችዬ - ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም. (April 20, 2009) \n kuchiye@gmail.com This e-mail address is being protected from spambots, you need JavaScript enabled to view it

ለጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃ ሙት መሆኔን ሀገር ያውቃል። የእርሱ ሙዚቃ ዳግም ላይሰማ ይታገዳል ያሉኝ ይመስል ከሰሞኑ መልሼ መልሼ የማዳምጠው እሱኑ ብቻ ነበር።

 

እንደኔ ሙዚቃን የሚያሻምድ ሰው ጥላሁን ለትውልዳችን የተሰጠ ልዩ በረከት፤ የዕምነታችንና የሁሉም ዓይነት ምኞታችን መገለጫ ነው ብሎ ከደመደመ ቆይቷል። አጋነንክ የሚል ከመጣም እስከመጨረሻው እሞግተዋለሁ እንጂ እንደ ሉሲና እንደ አክሱም ሐውልት ብሔራዊ ቅርሳችን ነው ባይ ነኝ። ለዚህ ይመስለኛል የጥላሁን ዜና-ዕረፍት እንደተሰማ ሚሊዮኖች በመብረቅ የተመታ ያህል ባሉበት የደረቁት፣ ያነቡትና የተከዙት።

 

የኔው ድንጋጤና ኀዘን ግን ወደ ፍስኀና ወደ ምስጋና ሲለወጥ ፋታ አልፈጀበትም። ልማድ ሆኖብኝ ሲከፋኝና ፍቅር-ፍቅር ሲለኝ ኮምፒዩተሬ ላይ ዘወትር በተጠንቀቅ የሚጠብቀውን የጥሌን ሙዚቃ ነው ጠቅ የማደርገው። ዛሬም ያንኑ አደረግሁና ወደ ትራክ ስድስት መራሁት። የሙዚቃው አጀማመር ገና ከመነሻው ምድርን ቃጤ የሚያደርግ ዓይነት ነው። በጣም የተሟሟቀ፤ የጥድፊያ ጥሪ ያለበትም የሚመስል … ጥሌን የሚጣራ የሚመስል። ወዲያው ተቀላቀሉ ጥሌና ሙዚቃ … ይለቀው ጀመራ ጥሌ በዚያ መረዋ ድምፁ! …

 

“… ያሳለፍነው ዘምን ደስታን ያየንበት … ተመልሶ ቢገኝ አሁን ምን አለበት?! …

 

እ … ህህ! … እህ … እህህ! … አይይይይ! …”

 

ይሄን ሙዚቃ ስንቴ እንደሰማሁት የሚያውቀው ፈጣሪ ብቻ መሆን አለበት። ጥላሁን እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ኖታዎችን አዋህዶ የዘፈነበትና የድምፁ ቅላፄ ጐልቶ የወጣበት በዚህ ዘፈን ይመስለኛል። ቢሮዬ ወዲያው ተሟሟቀ። ለቀቅሁት እኔም እንዳቅሜ … አጀብኩት ጥሌን። ቢሮዬ ውስጥ ማን ለሰማኝ? ምድረ ፈረንጅ “ምን ተፈጠረ?” ብሎ ቢመጣም በቂ ምክንያት አለኝ አልኩ። “የከበረና የተባረከ ሕይወትን እየተሰናበትሁ ነው” ካልኳችው እንደሚገባቸው አልተጠራጠርኩም። መቼም ፈረንጆች አይደሉም? ቀጠልን እኔና ጥሌ! … “እ … ህህ! … እህ … እህህ! … አይይይይ! …” አልን። ስንቱን ባነሆለለ ፈገግታው አየት ያደረገኝና “ቀጥል! ጥሩ ይዘሀል” ያለኝ መሰለኝ!” ምን ገዶኝና ማንን ፈርቼ? … ቀጠልኩ … የጥሌን ትዝታና ውለታውን በልቤ እየመዘገብሁ።

 

“ይሄ ነው እንጅ!” አልኩ፤ እንዲህ ነው እንጅ ጥሌን ማስታወስ! … 55 ዓመት ሙሉ የምድረ ሐበሻን ቤት በደስታና በፈንጠዝያ የሞላ፣ ያሳቀ፣ ያስደለቀ፣ መድረኮችን ያስጨነቀ፣ የወደደና ያዋደደ፣ …፤ ሽኝቱ በተለየ መሆን አለበት አልኩ። ልንሸኘው የሚገባው በትዝታ ቅኝት፣ በባቲ ለዛ፣ ባንች-ሆየ ቃና፣ በ“ሠላመካ” ዝማሬ መሆን አለበት ብዬ ወሰንኩ። የ“አልቻልኩም”ን ጀግና፣ የ“ይህ ነው ፍላጎቴን” መሪጌታ የምንሸኘው ከበሮው እየተደለቀ፣ ሳክሱ እየሳቀ፣ ትራንፔቱ እያማለለ ሊሆን ይገባል አልኩ።

 

ጥላሁን ዝንተ ዓለም አይረሳም። መሰል-የለሽ እንጉርጉሮዎቹን፣ ግርማ ሞገሱንና የእርሱ ብቻ የሆነ ለዛውን በውስጠኛው የምናባችን ክፍል አትሞብናልና። የዘመናችንን የኪነት የበህር ልጅ እንዴትስ ልንረሳው ይቻለናል?

 

በል ደህና ሁን ጥሌ! ከተለየኸን … ደህና ሁን!

 

\n Kuchiye@gmail.com

 

ይኼ ነው ጥላሁን

አብርሃም ሠለሞን ( \n slat6@yahoo.com This e-mail address is being protected from spambots, you need JavaScript enabled to view it )

(PDF)

ታላቅ የዜማ ሰው የወገን መመኪያ፣

ጥላሁን ገሠሠ ክብር ነህ ለኢትዮጵያ።

በስምህ በዝናህ ሁሉም ያከበረህ፣

ለሕፃን ለአዋቂው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነህ።

 

(ለክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ስለሀገር ወዳድነቱና ስለሠራው ድንቅ ነገር ሁሉ “ይበል!” የሚያሰኝ ድርጊት ነውና በጎልዳፋ ብዕር መልካም ስሙን ለማንፀባረቅ የተፃፈ ግጥም ነው። ይህ ግጥም በስኳር በሽታ ለሚሰቃዩ ወገኖቻችን ገንዘብ ለማሰባሰብ ክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በምድረ አሜሪካ ሚኒሶታ በሄደ ጊዜ ስለመልካም ግብሩ የተነበበለት ነው።)

 

የ ሙዚቃው ንጉሥ ጥላሁን ገሠሠ፣

ጥ ሎን ኮበለለ እንባ እያፋሰሰ

ላናየው ላያየን አመለጠን ድንገት፣

ሁሉን እርግፍ አርጎ በፋሲካ ሌሊት

ንብረትና ሀብቱ ህዝብ ነበር ለሱ፣

ገንዘብና ጌጡ መከዳ ትራሱ

ሰናይ ምግባር ይዞ አብሮን እንዳልኖረ፣

ሰው መሆን ከንቱ ነው ጥሎን ተሰወረ

ንገሩ ለሁሉም የንጉሡን መራቅ፣

ነገ ዛሬ አትበሉ ሀገር ህዝቡ ይወቅ

ፍለጋ አይወጣ ከኡኡታ በቀር፣

ስመ ጥሩው ዘፋኝ አመለጠ ከምድር

ይ ወደስ ይደነቅ ታምረኛ ድምፁ፣

ማራኪ ቁመናው አይነግቡ ገጹ

ርቱዕ አንደበቱ ታጥቷል እንደዘበት፣

ልዑል አምላካችን የዓለም ባለቤት፣

ንጉሥ ጥላሁንን አኑርልን ገነት

 

 


On Stage Tilahun
 

 
    Hosted and Designed by Yebbo Communication Network. www.yebbo.com (c) 2009